ሰላም ምርጦች

ዩትዩበር
ሥራ -ፈጣሪ
አሽሩካ እባላለው ዩትዩበር እና በሚድያ ስራ-ፈጣሪ ነኝ። በዋናነት የፍቅር ግኑኝነት እና ሕይወትን መለወጥ ላይ ያተኮሩ ቪድዮዎችን እሰራለው። ወግ የፍቅር ጨዋታዬ ማጣፈጫ ነው።
ችግርን መፍታት ላይ ካተኮሩት ቪድዮዎቼ በተጨማሪ ወቅታዊ የመዝናኛ ጉዳዮችን አዝናኝ በሆነ ሁኔታ እቃኛለው ሂስ እሰጣለው።
መረዳዳት ሐሳብን ከመካፈል እንደሚጀምርም አምናለው። ሐሳብ ትልቅ ጉልበት አለውና የማውቀውን አካፍላለው።
በሙያዬ ኬሚካል መሐንዲስ ነኝ። ለሁለት አመት ያክል በመንግስት ዩንቨርሲቲ ተቀጥሬ አስተምሬያለው። የማቴሪያል ምህንድስና የድህረ ምረቃ ኮርሶችን ወስጃለው። ስነ ፅሑፍ ያስደስተኛል ፤ ግጥም መፃፍም ውስጤ ነው። ማንበብ እወዳለው በተለይ ራስን መለወጥ ላይ ያተኮሩ መፅሐፍትን ማንበብ አዘወትራለው።
የሰውን ችግር ማድመጥ፤ ለሰው ጊዜ መስጠት እንደ ተፈጥሮ ስጦታዬ የምቆጥረው ነገር ነው። የተማርኳቸው፣ ማንበብ ማዘወትራቸውና የስነ ፅሁፍ ስጦታዬ ተዳምረው ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም እንዲሉ አሽሩካ ሚድያ ተወለደ። የፍቅር ሕይወታችሁን የሚለውጡ ሕይወታችሁን የሚያሳድጉና የሚያዝናናችሁ መረጃዎችን ማድረስ አላማው ነው።
ዩትዩብ ላይ እንድቆይ ያደረገኝ ዋናው ነገር በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ (አረብ ሐገራት) የሚገኙ ወገኖቼ የሚደርስባቸውን ጫናና ዘርፈ ብዙ የሕይወት ፈተና ማየቴ ነው። የነሱንና የሌሎች ወገኖቼን የሕይወት ጥያቄዎች መመለስ ላይ እና ማዝናናት ላይ በማተኮርም ወደ ሚድያው አለም ሰተት ብዬ ገባው። በርካቶችም ምስጋናቸው ደርሶኛል።
የሕይወቴ አቅጣጫ በዚህ አጋጣሚ ተቀይሯል፤ ሚድያ ላይ መስራት ምርጫዬ አድርጌያለው። የምሰራውንም ነገር በጣም እወደዋለው። እፅፋለው ቪድዮዎችን አቀርባለው።
የእሳት ዳር ጨዋታ ፣ ፍትፈታ ፣ ሳይንሱካ በአሽሩካ እና የአሽሩካ ካሜራ የተባሉ በወቅቱ የዩትዩብ ፕሮግራሞቼ ናቸው።
እና ምን ትጠብቃላችሁ ? 🙊🤣
ለሳቅ ለጨዋታ ለመማር ከመቀጡ
ወደ አሽሩካ ቤት ገብተው ይቀውጡ።
ድህረ-ገፄን ይከታተሉ ዩትዩብ ቻናሌን ይቀላቀሉ።
ምርጫችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለው።
መረዳዳት ሐሳብን ከማካፈል ይጀምራል!
የይቅርታ ልብ ለሁላችን!